ሥዕለ ኪዳነ ምሕረት


በድጋሚ እርማት ተደርጎበት የተለጠፈ።

በኃይለማርያም ሽመልስ

ኦርቶዶክሳውያን እንደ እግዚአብሔር ቸርነትና እና ቅዱሳን አማላጅነት መጠን በዚህ ጦማር በየቀኑ በዚህ የቅዱሳን ነቢያት ጾም ወቅት ልዩ ልዩ የሆኑ የቅዱሳን ሥዕላትን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ እንዲቀርብ የምትፈልጉት የቅዱስ ሥዕል ካለ በዚህ አድራሻ አሊያም በፌስቡክ ገጽ መጠየቅ ይቻላል፡፡

በዛሬው ዕለት የኪዳነ ምሕረት የምትከበርብት ዓመታዊ በዓል እንደመሆኑ መጠን በእመቤታችን የምሐረት ቃልኪዳን የተቀበለችበት ሥዕል ምስጢሩንና የሚታዩ ችግሮችን እንመለከታለን፡፡


ኪዳን የሚለው ቃል ተካየደ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ተማማለ፣ ተስማማ፣ ውል ገባ ማለት ነው፡፡ ኪዳነ ምሕረት ማለትም ደግሞ የምሕረት ቃል ኪዳን ማለት ነው፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ስለሰው ልጆች ይቅርታ የገባላት ኪዳን ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት፣ ለሚያከብሩት፣ ለሚወዱትና ለሚወዳቸው ሁሉ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ኪዳናትን ሰጥቷል፡፡[1]

‹‹የኪዳነ ምሕረት ሥዕል›› በመባል የሚታወቀው ሥዕል በቤተ ክርሰቲያናችን በስፋት ከሚሳሉት የወላዲተ አምላክ ሥዕል ጭብጦች ውስጥ አንዱ ሲሆን። ከሥር እንዴት እንደሚሣልና በዘመናችን የሚታየውን የሥዕል ስያሜ ማቀያየር እንመልከታለን።
ከጌታችን ኢየሱስ ቃልኪዳን ስትቀበል በጎሎጎታ የሚያሳየው ሥዕል አንደኛው ትክክለኛው ገላጭ ሥዕል ሲሆን፤ ይህ ሥዕል እንደ ቤተ ክርስቲያኑ ስፋት የሚጨመረው ጭብጥ ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ሥዕል ዘይቤ ላይ የሚታዩት መላእክት ቁጥራቸው ሊበዛ አሊያም ሊያንስ ይችላል፡፡ ይህ ሥዕል ላይ እመቤታችን እና ጌታችን ቆመው አሊያም ተቀምጠው ጌታችን በቅዱሳን እጆቹ የእናቱን ቅዱሳን እጆች በመያዝ ቃል ኪዳን ሲገባላት አሊያም በቅዱሳት እጁ ቃል ሲገባላት የሚያሳይ ዓይነት ሥዕል ነው፡፡

በዚህ መልኩ እመቤታችን ከተሳለችባቸው አብያተክርስቲያናት መካከል ጎርጎራ ደብረ ሲና(17ኛው መ.ክ.ዘ.)፣ አብርሐወ አጽብሐ (19ኛው መ.ክ.ዘ.)፣ አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ መቐለ(20ኛው መ.ክ.ዘ.)፤ ከጥንታውያን ብራና መጻሕፍት ከተመለከትን በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ግምጃ ቤት የሚገኘው የ17ኛው መ.ክ.ዘ. ተአምረ ማርያም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በዘመናችን በኪዳነ ምሕረት ሥዕል የሚታዩ ክፍተቶች

በዘመናችን ቅዱሳት ሥዕላትን በተመለከተ አንዱ ፈተና የቤተ ክርስቲያን የሥዕል ትውፊትን ሳያውቁ የሚሥሉና የሚያሥሉ አካላት መብዛት ነው። ለዚህ አንዱ ምሳሌ አንድን የቅዱስ ታሪክን አሊያም ቅዱሱንም ጨምሮ ወካይ ሥዕሎች እያሉ በሌላ የመተካት ክፍተቶች ናቸው።

ከእነዚህ መካከልም በዘመናችን በትክክለኛው ሥዕል የኪዳነ ምሕረት ታሪክ እየተገለጸ አይገኝም። ምክንያቱም አብዛኛው ምእመን እጅ በዚህ ሰዓት የሚገኙት ሁለት ሥዕሎች ሲሆኑ እነርሱም ሥዕለ ንግሣ እና በግብፅ ቤተ ክርስቲያን የመገለጧ እመቤት በመባል የምትታወቀው ሥዕሎች ናቸው።

1. ሥዕለ ንግሣ

ይህ ሥዕል አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሲያከብሯት ማለትም የክብር አክሊል ሲያቀዳጀዋት የሚያሰየው ሥዕል፡፡ ይህ ሥዕል በሁለት መልኩ በሥዕል ተገልጦ በስፋት ይተያል፡፡ የመጀመሪያው አብና ወልድ ተመሣሣይ ገጽ እና ነጭ የፀጉር ዓይነት ተደርጎላቸው ሲሣል፤ በሁለተኛው ሥዕል ላይ ግን ወልድ እግዚአብሔር ፀጉሩ ጥቁር ተደርጎ ይሠራል፡፡ የእግዚአብሔር አብ ሥዕል ላይ ግን ለውጥ አይደረግም፡፡ መንፈስ ቅዱስም በሁለቱም ዓይነት ውክልናዎች ላይ በርግብ አምሳል ሆኖ ይሣላል፡፡

የዚህ ሥዕል በስፋት መታየት የጀመረው በሁለተኛው የጎንደር የአሣሣል ዘመን(18 መ.ክ.ዘ.) ገደማ ሲሆን፤ በዘመኑ የነበረውን የነገሥታት አነጋገሥ በሚያሳይ መልኩ እመቤታችን የንግሥና ዘውድ (አክሊል) ሲደረግላት ይታያል።

የዚህ ምክንያቱም እመቤታችን ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ በመሆኗ ከቅድስት ሥላሴ በፍጥረት ዘንድ የንግሥትነትን ማእረግ አግኝታለች። መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት “ንግሥቲቱ በቀኝ ትቆማለች” እንዳለ መዝ 44። ይህንን ለማመልከት እመቤታችን የነገሥታት አነጋገሥን በሚጠቁም መልኩ ቅድስት ሥላሴ አክሊል ሲያደርጉላት ይሣላል።

ዳግመኛም በቀደመው ዘመን በሥዕሎቹ ላይም የሚጻፈው ገላጭ ጽሑፍም “ዘከመ አንገሥዋ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ (ሥሉስ ቅዱስ) ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ” የሚል ነበር። ገላጭ ጽሑፉም ሥዕሉ የንግሥናዋ እንጂ የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት እንዳልሆነ ጭምር ያስረዳናል።

ሆኖም ግን በዘመናችን ይህንን ካለመረዳት ይህንን ሥዕለ ሥዕለ ኪዳነ ምሕረት በማለት ሠዓሊያንም ጭምር ሲሥሉት ምእመናንም ሲጠቀሙበት እንመለከታለን። ይህ ተስተካክሎ በትክክለኛው ስሙ “ሥዕለ ንግሣ” በማለት እንዲጠቀሙበት ይገባል።

በዚህ ጭብጥ ከተሣሉ እበያተ ክርቲያናት መካከል መሐል ዘጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን (18ኛው መ.ክ.ዘ.)፣ ጨለቆት ሥላሴ (18 ኛው መ.ክ.ዘ.) ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ጭብጥ በስፋት በአሁኑ ዘመን ተሰራጭቶ እና የኪዳነ ምሕረት የሚባለው ሥዕል ነው፡፡

2. የመገለጧ ማርያም

በመጨረሻም በግብፅ ሀገር ባሉ ክርስቲያን ወገኖቻችን ‹‹የመገለጧ ማርያም›› በመባል የምትታወቀው የቅድስት ድንግል ማርያም በተለምዶ የኪዳነ ምሕረት ሥዕል በስፋት ይታወቃል፡፡ ይህ ታሪክም በዘይቱን በተባለ ቦታ እመቤታችን ልክ እንደ ደብረ ምጥማቅ በዘመናችን በመገለጥ ሕዝቦችን በሙሉ የባረከችበትን ተአምር ለማመልከት የተሣለ ነው። ይህ ሥዕል በግብፅ ሀገር በጣም ታዋቂ ሲሆን ምእመናንም ብዙ በረከት ያገኙበት ነው። ለአብነት የዘይት አፍላቂዋ ሥዕለ ማርያምን መጽሐፍ ይመልከቱ።

በእኛ ምእመናንም ዘንድም በስፋት በኪዳነ ምሕረት ሥዕል ስም በአገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል ነገር ግን ቅዱሳት ሥዕላት በሚወክሉበት ጭብጥ ማለትም የዘይቱኗ እመቤት በሚል ለአገልግሎት ቢውል ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ከአስተማሪነት አንጻር የተሻለ ይሆናል፡፡

http://zeitun-eg.org/warraq.htm

የወላዲተ አምላክ አማላጅነት በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ለዘላለሙ ፀንቶ ይኑር፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት እግዚአብሔር፡፡

ወለወላዲቱ ድንግል፡፡

ለመስቀሉ ክብሩ፡፡


[1] http://silemariam.blogspot.com/2010/12/blog-post_12.html

5 thoughts on “ሥዕለ ኪዳነ ምሕረት

  1. #አምላክ እግዚአብሔር ፦የቅዱስ ሉቃስ፡ የዮሐንስ ወንጌላዊ፡ የመብዓ ጽዮን፡ የኹሉ ቅዱሳን አምላክ ጸጋውን ያብዛልክ
    የቅዱሳኑንም ጸጋ በረከት(ሀብተ ሥዕለ አድኅኖ) ምጢሩንም ጨምሮ ያድልክ መምህሬ

    ቃለ ሕይወት ቃለ በረከት ያስማአይከ እኁየ
    (ቃለ በረከት ያስማአይከ ወመምርየ)
    በግብርከ ወልደ ተክለማርያም(መብአ🎁 ጽዮን)
    በስምከ ኃይለማርያም

    ሚሥጢር የሚጠነቅቅ (የምጠብቅም) ሥዕለ አድኅኖ ከማግኘታችን በተጨማሪም ትርጉሙን ከነማብራሪያው፣ ሥዕለ አድኅኖውም ከተሳለበት ቦታም ጭምር በማቅረብክ ከማስረጃ ከአምክኒዮ ጋር በጣም ያስምራል
    /**//የፊደሎችም አቀማመጥ፣ መልክአ ፊደልም የራሱ ትርጉም አለዋ🙂🤔🙌🙏//**/

    ጸጋውን ያብዛልክ
    ወዳጄ(መምህር
    ከዚህ በላይ የምታገለግልበት ዕድሜን ከጤና ጋር ያድልክ

    Like

  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን።
    በጣም የሚደንቅ ስራ ነው እየሰራህ ያለኸው። እግዚአብሔር ይባርክህ።

    Like

Leave a comment