የቅዱሳት ሥዕላት አላስፈላጊ ቦታዎች በጥምቀት በዓል መቀመጥ


በኃይለማርያም ሽመልስ

ይህንን ጽኹፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ በጥምቀት በዓል በዛሬው እለት የተመለከትኩት አዛኝ ከኦርቶዶክሳዊነት ፍጹም የራቀ ግን ባለማወቅ በየዋሕነት የሚደረግ ድርጊት ነው፡፡ ይህም የቅዱሳት ሥዕላት አላስፈላጊ ቦታዎች መቀመጥ ነው፡፡

ቅዱሳት ሥዕላት ልክ እንደ ታቦቱ፣ ጽንሐው፣ መቋሚያው፣ ከበሮው እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅዱሳት መገልገያ ሲሆኑ፤ የተሰጡንም በፈቃደ እግዚአብሔር እንድንባረክባቸው፣ እንደንቀደስባቸው እና እምነታችንን እንድንገልጽበቸው ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳት ሥዕላትን መንፈሳዊ ዓላማ በዓበይት ሦስት ምክንያቶች ትጠቀምባቸዋለች፡፡ እነዚህም፡-

1፡- ለሥርዓተ አምልኮ፡- ማለትም ለእግዚአብሔር መገዛታችንን የምንገልጽባቸው አንዱ መሣርያ ሲሆኑ፤ በጸሎት፣ በምህላ፣ በዝማሬ እና ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ላይ በመጠቀም አምልኮታችንን እንገልጻለን፡፡

2፡- ለማስተማሪያነት፡- ይኸውም እምነትን፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮችን የምናስተምርባቸው አንዱ መሣሪያዎች ሲሆኑ፤ በተለይ ማንበብ እና መጻፍ ለማይችሉ አማኞች ትልቅ ጥቅም ሲሰጡ ይገኛሉ፡፡

ethiopian-church-5932

3፡- ፍቅራችንን ለመግለጽ፡- አንድ ሰው የሚወደውን የቤተ ሰቡን ፎቶ በተለያዩ ቦታዎች በማስቀመጥ ናፍቆቱን እንደሚወጣ እኛም ‹‹የገነት መስኮቶች›› ተብለው የሚጠሩትን ቅዱሳት ሥዕላትን እንደ መስኮት በመጠቀም ቤተሰቦቻችን ቅዱሳንን እናይባቸዋለን፡፡ ናፍቆታችንንም እንወጣባቸዋለን፡፡ ሐዋርያው  ሀገራችን በሰማይ ነው እንዳለ እኛም ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌምን የምናይባቸው መብራቶች ቅዱሳት ሥዕላት ፍቅራችን ለመግለጽ እንጠቀምባቿለን፡፡

የቅዱሳት ሥዕላት ዓላማቸው ያልሆነው ደግሞ ለማስዋቢያነት ወይም ጌጥነት ነው፡፡

እነዚህ መንፈሳዊ ዓለማዎች ልክ እንደ ተዋሕዶ አይነጣጠሉም ማለትም አንድ ቅዱስ ሥዕል ማስተማሪያ አሊያም ለሥርዓተ አምልኮ ወይም ፍቅር መግለጫ ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉም ጥቅሞች በአንድነት ሳይነጣጠሉ በውሕደት አገልግሎት ይሠጣሉ፡፡ ስለዚህም አንድ ቅዱስ ሥዕል ፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ይሰገዳል፣ ይጸለያል፣ ትምህርት ይሰጣል እንዲሁም ለምእመናንን ቅዱሳንን መውደዳቸው እንዲገልጹ ይደረጋል፡፡

ሆኖም ግን ማንኛውም ቅዱስ ሥዕል ከእነዚህ አገልግሎት ውጪ አሊያም አንዱን ለብቻው ነጥለን የተጠቀምን ከሆነ በተገቢው መልኩ ቅዱሱን ሥዕል እየተጠቀምንበት እንዳልሆነ ያመለክታል፡፡ አለመጠቀም ብቻ ሳሆን በግብር መናፍቃንን እንመስላቸዋለን፡፡ ለምሳሌ አንድን ቅዱስ ሥዕል ለማስተማሪያነት ብቻ የምንጠቀም ከሆነ ለሥርዓተ አምልኮ በሥዕሉ ፊት እጣን የማይታጠን፣ ጸሎት የማይደርስ ስግደት የማይቀርብ ከሆነ፤ ልክ መናፍቃኑ ለትምህርቶቻቸው በሚጠቀሙባቸው ፊልሞች፣ መዝሙሮች እና መጽሐፍቶች ላይ እንደሚገቡት ሥዕሎች ይሆናሉ፡፡ ይህንን በመጽሐፋቸው እንደጣዖት የሚቆጥሯቸውን ሥዕል ለማስተማሪያነት ብቻ እንድነጠቀም ሲነግሩን እንመለከታለን፡፡[1]

ዳግመኛም ወደ ሀገራችን የሚመጡ ቱሪስቶች እንደሚገዟቸው የገበታ ሥዕሎች መንፈሳዊነታቸውን አስቀርቶ ለቤት ማስዋቢያነት ይውላሉ፡፡

በዘመናችን የጥምቀት አከባበር ላይ የምንመለከታቸው ቅዱሳት ሥዕላት ከዓላማቸው አንጻር እንዴት ይታያሉ?

በዓለ ጥምቀት ሲደርስ የቅዱሳት ሥዕላት አጠቃቀማችን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጉያ አፈንግጠው ለወጡ ፀረ- ቅዱሳት ሥዕላት በር የሚከፍት እየሆነ ነው፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በየቆሻሻዎችና በማይገባ ቦታ ተሰቅለው የፀሐይ ሐሩር የሌሊቱ ውርጭ እና አቧራ የሚፈራረቅባቸው  ቅዱሳን ሥዕሎች በዝምታ የዘመኑን ችግር ይናገራሉ፡፡

በየመንገዱ ከመለጠፍ በተጨማሪ በዚህ ዓመት ከታዘብኩት የጥምቀት በዓል ላይ በአብዛኛው የወጣቶች ቲሸርት ላይ የቅዱሳን ሥዕሎች መመልከት ችያለሁ፡፡ ይህ አቀማመጣቸውን ለሚመለከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ በዝምታ የማይታለፍ ጉዳይ ነው፡፡

ለታቦቱ ክብር ምንጣፍ አንጥፈን እየሰገድን የቅዱሳኑን ሥዕል ማክበር እንዴት ተዘነጋን? ዳግመኛም በአላቂ ጨረቅ ላይ አትሞ በመልበስ ሥዕሎቹን ማሳደፍ ምን ይባላል?

ይህን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ አስመልክቶ ከወንድሜ ከዲያቆን ተመስገን ጋር ባለፈው ዓመት ተነጋግረንበት ነበር፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ዲ/ን ተመስገን የመፍትሔ አቅጣጫ ያላቸውን እና እንዴት መጠቀም እንዳለብን ያነሳቸውን ነጥቦችን ከሥር በማስቀመጥ ጽሑፌን እቋጫለሁ፡፡

                          ቅዱሳት ሥዕላትን እንዴት እንጠቀምባቸው?

1. በፊታቸው ሻማ በማብራት
ሥዕሉ የልዑል እግዚአብሔር ከሆነ የእግዚአብሔር ብርሓንነት እናስባለን “እኔ የዓለም ብርሃን ንኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል” ይላል፡፡ አንድም ሻማ እየቀለጠ ለሌላው ብርሃን እንደሚሆን ጌታችንም እርሱ ሞቶ ለዓለም ሁሉ ሕይወት ሁኖናል፡፡ሥዕላቱ የቅዱስንም ከሆነ የቅዱሳኑን ብርሃንነት እናስታውሳለን ማቴ 15÷19
2. በመጋረጃ ተሸፍነው መቀመጥ አለባቸው
ሊቀ ነቢያት ሙሴ የኪሩቤልን ሥዕል በታቦቱ መክደኛ ላይ እንዲያስቀምጥ ነው የታዘዘው፡፡ ቅዱሳት ሥዕላትን በንጹሕ ስፍራ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ አሁን በመንገድ ላይ ተለጥፈው የምንመለከታቸው ቅዱሳት ሥዕላት ግን ለመንገድ ማስዋቢነት የተቀመጡ እሰኪመስል ድረስ አንዳንዶቹ በምስማር ያለቦታቸው ተመተው ሁሉ ስንመለከት በእውነቱ ምነው የሚያስተምር ጠፋ?ወይስ የሚሰማ ነው የጠፋው ?
3. በካህናት እጣን እየታጠኑ መቀመጥ አለባቸው፡፡
አሁን ግን በየመንገዱ የምንመለከታቸው ቅዱሳት ሥዕላት እንኳን በጎ መዓዛ ባላቸው ነገሮች ሊታጠኑ ይቅርና ቦታም አልተመረጠላቸው፡፡ በበረከት ፈንታ መርገም እንዳንቀበል መማር ይጠበቅብናል፡፡ ከሁሉም በፊት መቅደም ያለበት ትምህርት ነው፡፡

 ምንተ ንግበር( ምን እናድርግ) ?

ብዙ ጊዜ ስለ ሚፈጠሩ ወቅታዊ ችግሮች መነጋገር በእኛ ሀገር ደረጃ የተለመደ አይደለም ግን ሳይቃጠል በእርጥቡ ሳይርቅ በቅርቡ መነጋገሩ ይሻላል፡፡

1.ከበዓለ ጥምቀት ዋዜማ በፊት ለወጣቶች ስለ ቅዱሳት ሥዕላት አጠቃቀም የሚመለከታቸው አካለት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግበር ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል
ምክንያቱም ወጣቶች የሚሰሩት በመንፈሳዊ ቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ነው ቢሆንም ግን ምን እንደሚሠሩ ሊማሩና ሊያውቁት ይባል፡፡አባቶችም አስተምሩ ተምሮ ማስተማር እዳን መክፈልም ነውና፡፡ወጣቱ ቢማር ከዚህ የበለጠ. መሥራት ይችላል፡፡

2.ቅዱስት ሥዕላት አሳታሚዎችም ፤ አከፋፋዮች ላይ ስለ ቅዱሳት ሥዕላት ትምህርት ቢሰጣቸው
ቅዱስት ሥዕላት አሳታሚዎችም ፤ አከፋፋዮች ለገንዘብ ብቻ ባትሰሩ ለሃይማኖትና ለታሪክም ብትጨነቁ ምክንያቱም በገቢያ ላይ በብዛት የሚገኙት ሥዕላት ትውፉቱን ያልጠበቁ የምዕራባውን ሥዕላት ናቸው፡፡ በመምህራን በተለይም የሙያው ባለቤት በሆኑ ሊቃውንት የተገመገሙ ሥዕላትን አሳታሚዎችም ፤ አከፋፋዮች ለአገልግሎት በታውሉ፡፡ቅዱሳት ሥዕላቱ ወንጌልን የሚሰብኩ እንደመሆናቸው መጠን በጥንቃቄ ቢዘጋጁ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡

3.ከሊቃውንት ጉባኤ ጀምሮ ያሉ አባቶችም ቅዱስት ሥዕላት በልዩ ትኩረት የሚታዩበት መንገድ ቢመቻች
አንዳንድ ቦታዎች ቅዱሳት ሥዕላትንም የሚሸጡ አካለት የእምነቱ ተከታይ ያልሆኑ ናቸው፡፡ግን ቅዱሰት ሥዕላት የማን ናቸው?የጠቅላይ ቤተ ክህነትስ ሕግ ክፍል አያውቅ ይሆን? ኦረ ስንቱ ግን ምእመናን ሁላችንም ድርሻ አለንና የድርሻን እንስራ፡፡

4.መምህራነ ወንጌልም ስለቅዱሳት ሥዕላት አቀማመጥና አጠቃቀም ና አገልግሎታቸው በጉባኤያት ሰፊ ትምህርት ቢሠጡ መልካም ነው ፡፡
እኔ የሰሞኑን እይታየን ሳስቀምጥ እናንተስ ምን ታዘባችሁ? ቅዱሳት ሥዕላትስ የት ይቀመጡ? እንወያይበት በሩ ለአስተያትም ለሁሉ ከፍት ነው፡፡


ዋቢ መረጃ

[1] በውኑ በማርያም ማመን ይገባሃልን? 119፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ የሚያጠቁር የቅዱሳት ሥዕላት አጠቃቀም በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s