ሥዕለ ፍልሰታ ለማርያም


ውድ የዚህ ድረ ገጽ ተከታታዮች እንኳን ለደስተኛይቱ ክብርት ስለሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም የሥጋዋ ፍለሰት በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ለዛሬ ከቤተ ክርስቲያናችን እንደ ጠፈር ሰፊና እንደ ውቅያኖስ ጥልቅ ከሆነው የእመቤታቸን ነገረ ሕይወቷንና ተአምራቷን ከሚገልጡት ሥዕሎች መካከል ተወዳጅ የሆነውን የፍልሰታዋ ሥዕልን አጭር መግለጫ ከአሣሣሉ ጋር አቅርቤያለሁ፡፡ መልካም ንባብ

የእመቤታችን ፍቅሯ ጠዓሟ እና አማላጅነቷ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማታያስ እና ሌሎች ብፁዓን ጳጳሳት አባቶቻችንና ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ይኑር፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎች ምንጫቸው መጽሐፍ ቅዱስና አዋልድ መጻሕፍት ሲሆን፤ በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የተገለጠው እውነትም በጊዜ እና በቦታ ሳይወሰን ቅዱሳት ሥዕሎች ይሣላሉ፡፡ ከእነዚህ ሥዕሎች መካከልም የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰተ ሥጋዋ ሥዕል አንዱ ነው፡፡

ለዚህ ሥዕል መነሻ ታሪክ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ በትንቢት ተነግሮ በኋላ ትንቢቱ ሲፈጸም የተከሰተውና በትውፊት የተቀበልነው የአምላክ እናት የቅዱስ ሥጋዋ ከዚህች ምድር ወደ ሰማያት ማረግ ነው፡፡ ታሪኩም እመቤታችን ለሰዎች ልጆች ስትል በጥር 21 ቀን ከዚህ ዓለም ድካም አርፈች፡፡ ክፉዎች አይሁድም ሥጋዋን ሊያቃጥሉ ሽተው ነበር፡፡ ይህ እንዳይሆን ጌታችን ቅዱስ ሥጋዋን ወስዶ ገነት አኖረው፡፡

ሐዋርያትም ሱባኤ ቢይዙ ዳግም ቅዱስ ሥጋዋን ከገነት አምጥቶ ሰጣቸው በሰኔ 14 ቀንም ቀበሯት፤ በሰኔ 16 ቀንም እንደ ልጇ በሦስተኛው ቀን ተነስታ ያረገችበት ተአምራታዊ ተነሥታለች፡፡

በዚህን ጊዜም ቅዱስ ቶማስ ከሐዋርያት ጋር በአገልግሎት ምክንያት አልነበረም፤ ነገር ግን ደመና ጠቅሶ ሲሔድ እመቤታችን በብዙ መላእክት ተከባ በምስጋና ስታርግ ያገኛታል፡፡ እርሱም የጌታን ትንሣኤ (በመጀመሪያው መገለጥ) አመለጠኝ አሁንም የእመቤታችን ትንሣኤ አመለጠኝ በማለት አዘነ፡፡ እመቤታችንም እነርሱ ትንሣኤን አላዩም አንተ እንጂ ብላ ለምልክት እንዲሆን ሰበኗን ሰጠችው፡፡

ቅዱስ ቶማስም ወደ ሐዋርያት ሔዶ ስለ እመቤታችን ቢጠይቃቸው እረፍቷ በጥር ቀብሯ ደግሞ በነሐሴ ቢሉት፤ እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል በማለት ቅዱሰ ቶማስ ጠየቃቸው በዚህም ወቅት ቅዱሳን ሐዋርያትም ወደ መቃብሯ ሲሔዱ ቅዱስ አካሏን አጡት፡፡ በዚህን ጊዜ ቢደነግጡ ቅዱስ ቶማስ ሰበኗን አሳይቶ ወደ ሰማይ ማረጓን ነገራቸው፡፡ እነርሱም ሱባኤው ቢገቡ እመቤታችንን ተገልጣላቸዋለች፡፡

እኛም ኦርቶዶክሳውያን ይህንን ታሪክ በማሰብ በፍቅርና አንድነት የፍልሰታ ጾምን በጾም በነሐሴ 16 የፍልሰታ በዓሏን እናከብራለን፡፡ ከስርም የቤተ ክርስቲያን ሠዓሊያን በተለያዩ ዘመናት እንዴት የፍለስታ ሥዕሏን እንደሣሉ እንመለከታለን፡፡

የፍልሰታ ለማርያም ሥዕል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን

የፍልሰታ ሥዕል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእመቤታችን ሥዕሎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ በተለይ ከ17ኛው መ.ክ.ዘ. ወዲህ ይህ ሥዕል በሚዘጋጁ የብራና መጻሐፍት ላይ፣ የግድግዳ እና የገበታ ላይ መታየት ጀመረ፡፡ የፍልሰታ ለማርያም ሥዕልም በተለያየ መልኩ በየዘመናቱ እየተሣለ የተለያዩ ገጸ ባሕርያትን በማካተት ወዳለንበት ዘመን ደርሷል፡፡
የፍልሰታ ለማርያም ሲሣልም በተለያየ መንገድ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተሣለ ሲሆን ከእነርሱ መካከል ከሥር በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

1ኛ ጨረቃን የረገጠችው እመቤት

እመቤታችን ጨረቃን በእግሮቿ ረግጣ፣ በደመና ተጭና እና በቅዱሳን መላእክት ተከባ ስታረግ ይሣላል፡፡  ከዮሐ ራእይ 12 ላይ ያለችውን ፀሐይ የታቀፈች ጨረቃም የእግሮቿ መረገጫ የሆነችውን ንግሥተ ሰማይ ጋር ይገናዘባል፡፡

image

image

ስታንስብሊው ሆንያስኪ የተባሉ ምሁር ግን በምእራቡ ዓለም ከፍልሰታዋ ታሪክ በተጨማሪ ጥንተ አብሶ ሳይኖርባት በንጽሕና መጸነሷን (Immaculate Conception) እና መወለዷን እመቤታችን ጨረቃን ተጫምታ የሚያሳየውና የሚያመለክተውን ሥዕል ወደ በሀገራችን ባሉ ሠዓሊያን ሥዕሉ ላይ የተወሰኑ ለውጦች በማድረግ ኢትዮጵያዊ የፍልሰታ ሥዕል እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይህ እንዲታወቅ በቤተ ክርስቲያናችን ከ17ኛው መ.ክ.ዘ. በተሣሉ ሥዕሎች ላይ የፍለሰታዋ ሥዕል መሆኑን ይገልጻል እንጂ
ስለጽንሰቷ የሚገልጥ በሥዕሉ ላይ ጽሑፍ አለመታየቱ ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡

ይህ የምእራቡ ዓለም ተጽእኖም የሚታየው እመቤታችን በ17ኛው እና በ18ኛው መ.ክ.ዘ. የነበሩ ሠዓሊያን ሲሥሏት ፀጉሯ እያሳዩ መሆኑ ነው፡፡ ፀጉሯም ሲታይ በሁለት መልኩ ተሥሎ ይገኛል፤ አንደኛው በ17ኛው መ.ክ.ዘ. ወደ ትከሻዋ ቀጥ ብሎ የሚወርድ ሲሆን በ18ኛው መ.ክ.ዘ. ደግሞ ወደ ላይ ፀጉሯን አስይዛ ተሥላ ይገኛል፡፡

ሆኖም ግን አንዳንድ ሠዓሊያን በ17ኛውም ሆነ በ18ኛው መ.ክ.ዘ. እመቤታችንን ፀጉሯን በማከናነብ ሥለዋታል፡፡ በቀጣይም መ.ክ.ዘ. አሁን ያለንበት 21ኛው መ.ክ.ዘ. ጨምሮ ጸጉሯን አከናንበው የሚሥሉ ሠዓሊያን በስፋት ማየት ተችሏል፡፡

image

2ኛ. ለሐዋርያው ቶማስ ሰበኗን ስትሰጠው

ጨረቃዋን ረግጣ ከመታየት በተጨማሪም ለቅዱስ ቶማስ ሰበኗን ስትሰጠው አሊያም ቅዱስ ቶማስ ጋር ስትነጋገር የሚያሳየው ታሪክም በፍልሰታ ሥዕል ላይ ይታያል፡፡ ሐዋርያው ቶማስም በደመና ላይ ሆኖ ሰበኗን በመቀበል ላይ እያለ ወይም በስፋት ባይታይም ስታረግ እየተመለከት ይሣላል፡፡ ጨረቃ ሳትረግጥና በመላእክት እየተመሰገነች ሰበኗን ስትሰጠው ተሥሎ ይገኛል፡፡

image

ቅዱስ ቶማስ ከእመቤታችን ሰበኗን ከመቀበል በተጨማሪ ሐዋርያትን ስለ እመቤታችን ሥጋ ሲጠይቃቸው ቅዱስ ጴጥሮስ ሲቆፍር እና ሌሎቹ ሐዋርያት አጆቻቸውን በአግራሞት ፊታቸው ላይ አድርገው ተሥሎ በአንድ ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በመሐል ዘጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚታየው የፍልሰታ ለማርያም ሥዕል ነው፡፡

image

በዚህ የፍልሰታ ሥዕል ላይ የቅዱስ ቶማስ ሥዕል በተደጋጋሚ ተሥሎ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎች መለያ መገለጫዎቹ አንዱ የሆነውን አንድ ገጸ ባህርይ ከአንድ ጊዜ በላይ በአንድ የሥዕል ድርሰት ላይ መታየት ሲሆን፤ በሥዕሎቹ ላይ ይህ መታየቱ ደግሞ ቅዱሳት ሥዕላት በጊዜ እና ቦታ የማይወሰኑ በመሆናቸውና እንዲሁም ዓላማቸው በግልጽና በአጭር መልኩ ቋንቋ ሥነ መለኮታዊ እውነታን ማስረዳት በመሆኑ ነው፡፡

3ኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ እመቤታችንን ሲማጸን

ቅዱስ ጊዮርጊስ እመቤታችንን ፍልሰቱን ከፍልሰታዋ እንድትደምረው ሲማጸን በፍልሰታዋ ሥዕል ላይ ተጨምሮ ይሣላል፡፡ ይህ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቅዱስ አጽሙ በነሐሴ 16 ቀን በታላቅ ደስታ ከፋርስ ወደ ልዳ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን መፍለሱን ያስታውሳል፡፡

በስንክሳር ላይም እንደተጠቀሰው እርሷን የሚወዱና በእርሱ ስም ለሚጸልዩ ለሚማጸኑ የድኅነት መንገድ እንዲሆናቸው የእርሱን ሥዕል ከእርሷ ሥዕል ጋር አብረው ይሥላሉ፡፡

ይህንን በሚገልጽ መልኩ የፍልሰታ ለማርያም ሥዕል የተሣለ ሥዕል በመሐል ዘጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሰማዕቱ የክብር ልብሶ ‹‹ምሰለ ፍለሰትኪ ደምርኒ እሙ›› ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት፡፡

ሌላኛው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል በ1964 በአለቃ በርሔ ገብረ ኪዳን የተሣለውና በኢየሱስ ጸሒ (Iyasus Tsahi) የሚገኘው የፍልሰታ ሥዕል ላይ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕትነት ሲቀበልና 7 አክሊላትን ሲውርዱለት እና ‹‹ምሰለ ፍለሰትኪ ደምርኒ እሙ›› በማለት ሲማጸን ይታያል፡፡

image

ይህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል በ17ኛው እና በ18 መ.ክ.ዘ. ይታይ ከነበረው የእመቤታችን የፍልሰታ ሥዕል በጭብጥ አዲስ ጭማሪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በስፋት አይታይም፡፡

ምንጭ

Chojnaski, Stanislaw. (1983) Major Themes in Ethiopian Painting; Indigenous Developments, The Influence of Foreign Models and Their Adaptation from the 13th to the 19th century, Wiesbaden: Franz Steiner Verlagh Gmbh.

Michael Gervers. Mazgaba Seelat: Treasury of Ethiopian Images.   

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s