በግዞት እያለ ነፍሡ ከሥጋው ተለይታ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እቅፍ ስትኖር

የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሥዕል በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን


ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ምስጢሮችን ያዘሉ መጻሕፍትን ጽፎ ያበረከተና በግንቦት 12 ቀን ያረፈ ቅዱስ አባት ነበር ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም እርሱ የደረሳቸውን መጻሕፍቶችን ለተለያዩ አገልግሎቶች ስትጠቀምባቸው ትኖራለች፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ስለ ሊቁ ሥዕል በዚህ ዘመን የተመለከትኩትን ችግር እና ለችግሩ መፍትሔ እንዲሆን በማሰብ የግንዛቤ መፍጠሪያ ጽሑፍ ሥዕሉን  በማስተባበር ከሥር ቀርቧል፡፡

ስለ ቅዱሳት ሥዕላት የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት ethioicons.wordpress.com እና facebook.com/ethioicons ይመልከቱ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እና ቅዱሳት ሥዕላት

ብሩክ የሚሆን ቅዱስ ዮሐንስ የሐዋርያው ጳውሎስን መልእክታትን ከመጠን በላይ ይወድ ነበር፡፡ በሕይወትም ሳለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሐዋርያውን የቅዱስ ጳውሎስ ሥዕልን አንዳንድ ጊዜ ከድካም በሚያርፍበት ቦታ ያስቀምጥ ነበር፡፡ መልእክታቱን በሚያነብበትም ወቅት ሥዕሉን በፊቱ አድርጎ እና ሐዋርያው አጠገቡ በአካል እንደተገኘ በማድረግ ይናገር፣ እርሱንም ያመሰግነውና ሐሳቡንም በሙሉ ወደ እርሱ ያደርግ ነበር፡፡[1]

ከዚህም ባሻገር ሊቁ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከልም ስለ ቅዱት ሥዕላት ክብር የሚጠቀስ ነው፡፡ በ8ኛው መ.ክ.ዘ. ለቅዱሳት ሥዕላት ሊሰጣቸው ስለሚገባው ክብርና በክርስትና ውስጥ ሥዕላትን መጠቀም አይገባም ይገባል በሚለው ውዝግብ ምክንያት በተጠራ አንድ ጉባኤ ላይም ለቅዱሳት ሥዕላት ተገቢ የሆነ አክብሮት እንደሚገባቸው የሚገልጽ ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት የተገኘ ምንባብ በተነበበ ጊዜ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ጳጳስ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥዕላትን በተመለከተ እንዲህ ከተናገረ ከእርሱ በተቃራኒ ይናገር ዘንድ ማን ይችላል›› ብሎ አሰምቶ ተናገረ፡፡[2]

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥዕል የሚታየው ችግር

አሁን ባለንበት ዘመን መረጃ ከብርሃን ፍጥነት የመረጃ መረብን ተጠቅሞ ሲተላለፍ ምእመናን በቀላሉ ስለ ቅዱሳን ታሪክ ለማወቅ እና በቀደመው ዘመን የነበሩ ሰዎች በአካል ለመሔድ ይቅርና በዓይን ምስላቸውን (ፎቷቸውን) ለማየት ያልታደሉትን ቦታዎች መረጃ መረብንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ተጠቅመው ለማወቅ አስችሏቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቅዱሳኑ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ሥዕላቸውም በቀላሉ ተደራሽነቱ ጨምሯል፡፡

ይሁን እንጂ በመረጃ መረብ ይሁን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ከምንመለከታቸው አንዱ የቅዱሳት ሥዕላት ችግር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የጠበቁ ቅዱሳት ሥዕላት በስፋት ያለመታየት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኛው ምእመን የሚጠቀሙባቸው የአንዳንድ ቅዱሳን ወካይ ሥዕሎች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የጠበቁ ያለመሆኑ ነው፡፡

ለዚህ ማሳያ ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥዕል ሲሆን፤ የዚህ ታላቅ አባት ሥዕል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና የግድግዳ ሥዕሎች ላይ የተሣለ ሆኖ ሳለ ሥዕሉ የማይገኝ ይመስል የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ሥዕሎች ምእመናን ሲጠቀሙ ይታያል፡፡

ይህ ቢሆንም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥዕላቸው ተሥሎ ለአገልግሎት ከዋሉት ቅዱሳን የሚመደብ ሲሆን፣ ሥዕሉ በስፋት ከተሣለባቸው እስኬማ መከከል፡-

  • ጽንሐ እና መስቀል ይዞ
  • ለአሥር ዓመት መልአከ ሞት ሲያቆም ያቆመበት ታሪክ፣
  • ንግሥት አውዶክስያን የመበለቲቱን ንብረት በጉልበት በቀማችበት ጊዜ ሲገጽጻት፣
  • ንግሥቲቱን በመገጸጹ ምክንያት በግዞት ሲሰደድ እና
  • በግዞት እያለ ነፍሡ ከሥጋው ተለይታ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እቅፍ ስትኖር የሚያሳዩት ሥዕሎች ይጠቀሳሉ፡፡

እኛም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የጠበቁትን ሥዕሎች ለመጠቀም የቅዱሱ ጸሎትና ምልጃ አይለየን፡፡


ለአሥር ዓመት መልአከ ሞትን ያቆመበት ታሪክ 

. . . አንድ ቀን ዮሐንስ አፈወርቅ አንዲት ሕፃን ልጅን ክርስትና ሊያነሳ ሲሄድ መልአከ ሞት ደግሞ ሕፃኗን ሊቀስፍ ሲሄድ በመንገድ ላይ ተገናኙና ዮሐንስ ‹‹ወዴት ትሄዳለህ?›› አለው፡፡ መልአከ ሞቱም ‹‹ሕፃኗን በሞት ቅሰፍ ተብዬ ተልኬ ልቀስፍ እየሄድኩ ነው›› አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹ሳትጠመቅና ልጅነትን ሳታገኝ እንዳትቀስፋት እስካጠምቃትም ድረስ እንዳትንቀሳቀስ›› ብሎ በሥልጣነ ክህነቱ አስሮት ሄደና ሕፃኗን ካጠመቃት በኋላ እረስቶት በሌላ መንገድ ተመለሰ፡፡

መልአከ ሞቱም በዮሐንስ ሥልጣነ ክህነት ታስሮ 10 ዓመት እንደቆመ ቆይቷል፡፡ ከ10 ዓመት በኋላ ዮሐንስ በዚያ መንገድ ሲያልፍ መልአከ ሞትን ቆሞ ሲያየው ‹‹ለምን ጉዳይ ቆመሃል?›› አለው፡፡ መልአከ ሞትም ‹‹የዛሬ 10 ዓመት አንተ ስትሄድ እንዳትንቀሳቀስ ስላልከኝ ሥልጣንህ እንደሰንሰለት አስሮ ይዞኛል›› ቢለው ዮሐንስም ይህን ያህል ጊዜ በመርሳቱ ተጸጽቶ ‹‹ተሳስቻለሁ በል ሂድ ግብርህን ፈጽም›› ብሎት መልአከ ሞትም ሄደና ልጅቱን ቀስፎ ዐርጓል፡፡ ዮሐንስም እቦታው ሲደርስ ቤተሰቦቿ ሲያለቅሱ ቢያገኛቸው አስጽናቷቸው ተመልሷል፡፡ . . .[3]

ምንጭ

[1] Taken word for word from the Life of St John Chrysostom. Mary H. Allies. Jhon Damascene on holy Images, Apologia of St. John Damascene Against Those Who Decry Holy Images Part One. 51-52.

[2] ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ።ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ። 85

[3] ከገድላት አንደበት ፌስቦክ ገጽ በግንቦት 12 ቀን የተጎበኘ

Images from Mazgaba Seilat 

Photos Copyright © 2005 Michael Gervers, Ewa Balicka-Witakowska 

ኃይለ ማርያም ሽመልስ፡፡ ግንቦት 2008 ዓ.ም. ተጻፈ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s