ጣዖትና የረከሱ ሥዕላት የተኞቹ ናቸው?


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ርኩሳን ሥዕላት ወይም ጣዖታት በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በታሪክ መዛግብት የተጠቀሱና አሁን ባለንበት ዘመንም ከሚታዩ የስእል ዓይነቶች አንዱ ሲሆኑ ውድ አንባቢያን ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ጽሑፍ ስለርኩሳን ሥዕላት ምንነት፣ ዓይነትና እነርሱን በተመለከተ ከአንድ ክርስቲያን ምን እንደሚጠበቅ ነው፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

መግቢያ

በመጀመሪያ ርኩሳን ሥዕላት ምን እንደሆኑ ለመረዳት ሥዕል ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ሥዕል›› በቁም መልክ፣ የመልክ ጥላ፣ ንድፍ፣ አምሳል፣ ንድፍ በውኃ፣ በመጽሔት፣ በጥልፍ፣ በስፌት ወይም በቀለም በወረቀት ገዝፎ ተጽፎ ከደብር፣ ከእብን፣ ከእጽ፣ ከማዕድን ታንጦ፣ ተቀርጦ፣ ተሸልሞ፣ አጊጦ የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ነው፡፡›› አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በማለት ሲያስቀምጡ የደማስቆው ሊቅ ዮሐንስ ደግሞ ‹‹ሥዕል ውክልና ሲሆን በውስጡ የተመሰለውን (የተወከለውን) ባለቤት የያዘ: ነገር ግን ከተወከለው ከባለቤቱ ጋር ግን የተወሰነ ልዩነት አለው፡፡›› በማለት ያብራራዋል፡፡

ሥዕል ነጠላ ሲሆን ሥዕላት ደግሞ ብዛት ያመለክታል፡፡ በአጠቃላይ ሥዕል እና የሥዕሉ ባለቤት ማለትም በሥዕሉ የተወከለው ባለቤት ተመሳሳይነትና ልዩነት አላቸው፡፡ ተመሳሳይነታቸው ከላይ እንደተገለጸው ሥዕል የአንድ ነገር መልክ፣ የመልክ ጥላ፣ ምሳሌ (አምሳል) ወይም ውክልና ቢሆንም በውስጡ ግን የተመሰለውን (የተወከለውን) ባለቤት የያዘ በመያዙ ነው፡፡

ስእል ውክልና አምሳያ መሆኑን ከተገነዘብንና የሚወከል አካል መኖርኑን ከተረዳን ዘንድ ከሥር ርኩሳን ስእላት ምንነትና ዓይነት እንመልከት፡፡

ርኩሳን ስእላት ወይም ጣኦታት ምንድን ናቸው?

ርኩሳን ሥዕላት በመጽሐፍ ቅዱስ የሚባሉት በተለያዩ መልኮች የሚሣሉ ሆነው የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ የሚቃወሙና በተቃራኒው ደግሞ የሰይጣንን ክፉ ተግባራት የሚያወድሱት በሙሉ ናቸው፡፡ በዚህ ዘመንም የጣዖት አምላኪዎች የሚጠቀሙባቸው ሥዕሎች፣ የአምልኮ ምልክቶች እና ጽሑፎች እና ወዘተ. . . ከዚህ መደብ ይገባሉ፡፡ እነዚህ የረከሱ ሥዕላት ወይም ጣዖታት በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በታሪክ መዛግብት የተጠቀሱና አሁን ባለንበት ዘመንም ለተለያዩ አገልግሎት ሲውሉ ከሚታዩ ስእሎች ዓይነቶች አንዱ ናቸው፡፡

ርኩሳን ስእላት በመጽሐፍ ቅዱስ

በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚገኙ ርኩሳን ሥዕሎች መካከል እስራኤላውያን በጥጃና በተለያዩ እንስሳት ምስል ሰርተው ያመልኳቸው የነበሩት ዘፀ 32፡1-10፣ ናቡከደነጾር በባቢሎን አውራጃ በዱር ሜዳ አቁሞት የነበረው ከወርቅ የተሠራ ምስል ዳን 3፡1፣ እና ከነዓውያን ያመልኳት የነበረችው ‹‹ አስታሮት›› የተባለችው የሴት ምስል ወዘተ. . . የመሳሰሉት ርኩሳን ሥዕላት ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህን ርኩሳን ሥዕላት ተብለው ለመጠራታቸው ዘዳ 7፡25፤ 1ኛ ነገ 12፡28-30፤ ዳን 11፡31፤ 12፡11፤ ማቴ 24፡15-18 መመልከት ይቻላል፡፡

ርኩሳን ስእላት በዘመናችን ‹‹ቀያይ ሰይጣኖች›› እንደማሳያ

በዘመናችን በማወቅና በግልጽ ሰይጣንን ከሚያመልኩ ሰዎች በተጨማሪ የተለያዩ አካላት በማወቅም ይሁን በየዋሕነት የረከሱና የሰይጣንን ክብር ከፍ የሚያደርጉ፣ ሰይጣንን በበጎ መልኩ የሚወክሉና በስም በማስታወቂያ መለያ፣ በዓርማ ላይ እና በሌሎች መልኩ ሥዕሉን የሚጠቀሙ ሰዎች ይገኛሉ፡፡

በዚህ ጽሑፍ ላይ ለማስተማሪያነት እንዲሆን ‹‹ቀያይ ሰይጣኖች›› በመባል ስም የተሰጣቸውን አካላት እንመልከት፡፡ በዚህ ክፉና በረከሰ ስእል የተለያዩ ነገሮች ሲወከሉ ዘመናት በሒደት አልፈዋል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ስም ከተወከሉ መካከል ሰዎች፣ ቦታዎች፣ እንስሳት፣ የልብ ወለድ ገጸ ባሕርያት፣ የዘፋኞች ቡድን፣ የሚጠጡ መጠጦች እና የስፖርት ቡድኖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡[1]

ትንሹ ቀይ ሰይጣን በመባል የሚታወቀው የልብወለድ ገጸ ባሕሪ
ቀይ ሰይጣን በመባል የሚታወቀው መጠጥ

ከእነዚህ መካከል በሀገራችን በስፋት የሚታወቀውና በብዙ ስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ የሚወደደው የማንችስተር ዩናትድ የእግር ኳስ ቡድን የረከሰውን የዲያቢሎስን ስእል በመጠቀም የሚታወቅ ነው፡፡ የዚህ ቡድን መለያ ዓርማ ስንመለከት ከመሐከሉ ዲያቢሎስ በቀይ ቀለም ትልቅ ሹካ ይዞ ይታያል፡፡ ይህ ዓርማንም እንደ ቤተክርስቲያን ትምህርት ብንመለከተው የረከሰ ጣኦት የሆነና ክርስቲያኖች  በሙሉ ለአገልግሎት እንዳይጠቀሙበት ነው፡፡

ነገር ግን በብዙ ሰዎች ክርስቲያኖችን ጨምሮ በኩራትና በደስታ ስሙን ‹‹ቀያይ ሰይጣኖች›› በማለት ሲጠሩት፣ ዓርማውን ለብሰውት ሲዞሩ ይባስ ብሎም ሲስሙት ይታያል፡፡

ከአንድ ክርስቲያን ምን ይጠበቃል?

ይህ ዓይነት ድርጊት ግን ፈጽሞ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላና የረከሰ ነው፡፡ በመሆኑም ለየትኛውም አገልግሎት መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡ ቅዱስ ቀለሜንጦስ ዘእስክንድርያም በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች የጣኦት አምላኮችን ሥዕሎች በማኅተማቸው ለሚያኖሩ፣ በጎራዲያቸው እና በጦሮቻቸው የጦርነት አምላክ የተባለችውን ጣዖት ለሚሥሉ እንዲሁም በዋንጫዎቻው ላይ የባኮስ ሥዕልን የሚጠቀሙትን ሲገስጽ እንመለከታለን፡፡

በተዘዋዋሪ ግን ምን ዓይነት ሥዕሎችን መጠቀም እንዳለብን ሲያስረዳ፡-

‹‹We are permitted to have a ring to make a seal. The images engraved on it and which we use as seal should be preferably be a dove, fish or a ship. . . .  ማኅተም ለመስራት ቀለበት እንዲኖረን ተፈቅዶልናል፤ በላዩ ላይ የሚሣሉት እና እንደማኅተም መጠቀም ያለብን ስእሎች ደግሞ ርግብ፣ ዓሣ አሊያም የሚወለበለብ ወይም በፍጥነት የሚቀዝፍ መርከብ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ . . . . ዳግመኛም በባሕር ዳርቻ ያሉ የዓሣ አጥማጆችን ስእል አንድ ሰው መጠቀም ይችላል፤ ይኸውም ሐዋርያትንና በትምህርታቸው የዳኑትን ክርስቲያኖችን ያስታውሰናል፡፡ [2]

እኛም እንደ ክርስቲያኖች መጠቀም ያለብን የተቀደሱን የተለዩትንና የእግዚአብሔር የሆኑትን እንጂ የረከሱትን ስእላት መሆን የለበትም፡፡ ምንም እንኳን ለአምልኮ ባንጠቀምባቸውም የስእላቱ ባለቤት የክርስቶስ ተቃዋሚ የሆነ ሰይጣንና ጣኦት መሆኑ በራሱ አምላካችን እግዚአብሔርን የሚያሳዝንና ጸያፍ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

© በኃይለማርያም ሽመልስ ታህሳስ 2008 ዓ.ም. ተጻፈ፡፡

ምንጭ


[1] https://en.wikipedia.org/wiki/Red_Devil

[2] Leonid Ouspensky. Theology of the Icon. Volume I. 36.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s