ሥዕል 18 ኛው መ.ክ.ዘ. የተሠራ የቅድስት ድንግል ማርያም እና ለወዳጇ ዘካርያስ ያደረገቸውን ተአምር የሚያሳይ ሥዕል

ለእመቤታችን ሥዕል ከነበረው ፍቅር የተነሣ ጽጌረዳ ለሚሰጣት ለዘካርያስ የተደረገ ተአምር


ከሮም ነገሥታት ወገን የሆነ ስሙ ዘካርያስ የሚባል አንድ ጎልማሳ ሰው ነበር፣ ከእለታት አንድ ቀን ከቤተክርስቲያን ገብቶ በእመቤታችን ፊት ሲጸልይ ከሥዕሏ ማማር የተነሳ ደስ አለውና ለዚች ሥዕል ምን ዓይነት እጅ መንሻ ላቅርብላት እያለ ሲያወጣና ሲያወርድ፣ ወራቱ የጽጌሬዳ ወራት ነበርና 50ውን የጽጌሬዳ አበባ ወስዶ ዘውድ አስመስሎና አክሊል ሰርቶ ከሥዕሏ ራስ ላይ በክብር አቀዳጃት፡፡

ይህ ሰው እንደዚህ እያደረገ ሲጸልይ ከቆየ በኋላ፣ የጽጌሬዳ ወራት ባለፈ ጊዜ ግን ለሥዕሏ ክብር የሚያቀርብላት የጽጌሬዳ አበባን በማጣቱ፣ እጅግ አዝኖ ወደ ቤተ-ክርስቲያን ሔደና በሥዕሏ ፊት ቆሞ እመቤቴ ማርያም ሆይ የጽጌሬዳ ወራት እንደላፈ አንቺ ታውቂያለሽና በ50ው የጽጌሬዳ ፋንታ ሰላምታሽን 50 ጊዜ እጸልያለሁ በማለት እንዲህ አለ፣ እመቤቴ ማርያም ሆይ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ እያለ በየቀኑ ሲጸልይ ኖረ፣ ከዕለታት አንድ ቀን ግን ይህችን ጸሎት ሳያደርስ ወደ አንዲት ሀገር ለመሄድ መንገድ ጀመረ።

ሥዕል 18 ኛው መ.ክ.ዘ. የተሠራ የቅድስት ድንግል ማርያም እና ለወዳጇ ዘካርያስ ያደረገቸውን ተአምር የሚያሳይ ሥዕል
ሥዕል 18 ኛው መ.ክ.ዘ. የተሠራ የቅድስት ድንግል ማርያም እና ለወዳጇ ዘካርያስ ያደረገቸውን ተአምር የሚያሳይ ሥዕል

በመንገድም እያለ ይህቺን ጸሎት እንዳላደረሰ አስታውሶ፣ ጉዞውን አቋርጦ ከመንገድ ወጣ ብሎ እንደቀድሞው እየሰገደ ሰላምታዋን ሲጸልይ፣ በእያንዳንዱ ሰላምታ ከአፉ የጽጌሬዳ አበባ ሲወጣና አበባው 50 እስኪሞላ ድረስ፣ የጽጌሬዳውን አበባ እመቤታችን ከአፉ እየተቀበለች በክንዷ ስታቅፍ፣ በአካባቢው የነበረና የሽፍቶች አለቃ የሆነ አንድ ሰው ይህን አይቶ፣ ጸሎቱን እስኪጨርስ ድረስ ከአፉ የሚወጡ ጽጌሬዳዎችን ይቆጥር ጀመረ።

ዘካርያስም ጸሎቱን ሲጨርስና አበባዎች 50 ሲሞሉ እመቤታችን ባርካው ወደሰማይ ስታርግ ይህ የሽፍቶች አለቃ አይቶ፣ እጅግ አደነቀና ጓደኞቹን ጠርቶ የጌታን ተአምር ታዩ ዘንድ ኑ ተብሎ እንደተጻፈ መዝ 45፡8 ልዩ ተአምር ኑ እዩ ብሎ ወደ ዘካርያስ ወሰዳቸው።

ሽፍቶችም ሔደው ዘካርያስን ይህ ተአምር ምንድን ነው ብለው ጠየቁት፣ እሱም እኔ ኃጢአተኛ ከመሆኔ በቀር በጎ ሥራ የለኝም፣ ነገር ግን የሰማይና የምድር ንጉሥ የሆነ አምላክን በድንግልና የወለደችው ድንግል ማርያምን እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ እያልኩ 50 ጊዜ ሰላም እላታለሁ አላቸው፣ በዚህ ጊዜ ሽፍቶቹ ደስ ብሏቸው ዘካርያስን ሸኙት፣ እነሱም ከዚህች ቀን ጀምረው ከክፉ ሥራቸው ተመልሰውና ወደ ገዳም ሄደው በምንኩስና ሕይወት ተወስነው ኖረዋል።[1]


[1]  ተአምረ ማርያም፡፡ ትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ 719-723፡፡ ሊቀ ጠበብት አስራደ ባያብል፣ ማኅሌተ ጽጌ ታሪክና ትርጉም ክፍል 1።24፡፡

 

Advertisements

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s