በአቡነ መብአ ጽዮን የተሣለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል

ሠዓሊ እና ቅዱስ አቡነ መባዓ ጽዮን (ተክለ ማርያም)


በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ልጅ በማጣታቸው በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ከሚለምኑ ሀብተ ጽዮንና ጽዮን ትኩና አቡነ መብዓ ጽዮን ተወለዱ፡፡ የንቡረ ዕድ ሳሙኤል ረባን ወገን የሆነው መብዓ ጽዮን አባቱ እስከ ዳዊት ያለውን ትምህርት አስተማረውና ዲቁና ተቀበሉ፡፡ በሌላኛው ስማቸው ተክለ ማርያም ይባላሉ፡፡ ጻድቁ እመቤታችንን ከሕፃንነታቸው ጀምረው እጅግ ይወዷት ነበር፡፡ click for pdf.

ትንሽ ልጅ ሳሉ አንድ ካህን ወደ ሀገራቸው በእንግድነት መጣና አባታቸው ሀብተ ጽዮን አሳደሩት፡፡ እንግዳውም ካህን የእመቤታችንን ሥዕል ምስለ ፍቁር ወልዳን ይዞ ነበር፡፡ ሲተኛም በራስጌው ያኖራት ስለነበር በሀብተ ጽዮንም ቤት አድሮ ጠዋት ተነሥቶ ሲሄድ የእመቤታችንን ሥዕል በራስጌው እንዳኖራት እረስቶ ሄደ፡፡

13 th Century Ethiopian Painting of the Theotokos Holy Virgin Mary

ያንጊዜ ሕፃን የነበሩት አባ መብዓ ጽዮንም ሥዕሏን ወስደው ሳሟት፣ በእርሷም ደስ ተሰኙባት፡፡ ለሌላም ሰው አልሰጥም ብለው በአንገታቸው አሰሯት፡፡ ሀብተ ጽዮንም ‹‹ይህችን የእግዳው ካህን ንብረት የሆነች የእመቤታችንን ሥዕል ከቤት እንዳላስቀምጣት ኃጢአት ይሆንብኛል እንዳልሰጠውም ከየት አገኘዋለሁ›› እያለ ሲቀጨነቅ ከዕለታት በአንደኛው ቀን ያንን እንግዳ አገኘው፡፡ ባገኘውም ጊዜ ከቤት የተዋትን የእመቤታችንን ሥዕል እንዲወስድ ነገረው፡፡

መጀመሪያ ሕፃን መብዓ ጽዮን እንዳገኛትና በጣም እንደወደዳት ለሌላ ሰውም አልሰጥም ብሎ በግድ ቀምቶ እንዳስቀመጣት ነገረው፡፡ እንግዳውም ይህን ሲሰማ ‹‹የሥዕሊቱ ባለቤት እርሷ የሕፃኑ እንድትሆን ፈቅዳለታለች፤ ከእኔ ዘንድ መሆኗን ፈቅዳ ቢሆንማ ኖሮ ባልተረሳችኝ ነበር ለዚያ ላገኛት ልጅህ የተገባች ናት›› ካለው በኋላ እርስ በእርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጥተው ተለያዩ፡፡

አባቱም በልጁ ላይ ስለሆነው ስጦታ አደነቀ፤ ሕፃኑ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የዳዊትን መዝሙርና የሕግን መጻሕፍት ሁሉ ያስተምረው ጀመረ፣ ዲቁና ተሾመ፡፡ በሥራውም ሁሉ ልበኛና ጥበበኛ የዜማውም መዓዛ የጣፈጠ እንደሆነ ባየ ጊዜ ቅኔን ይማር ዘንድ የዮሐንስ ደብር ወደምትሆን ወደ ደብረ ማርያም ወሰደው፡፡ የአንደገባጦንንም አውራጃ ሁሉ የሚገዛ መምህር በዚያ ነበረ፤ መባዓ ጽዮንንም ለሱና ለአንድነቱ መነኮሳት አደራ ሰጠው፡፡

አባ ስምዖንና አባ አዝቂርም ስምህ ማነው ብለው ጠየቁት፣ መባዓ ጽዮን ነው አላቸው፡፡ ከመምህራን ሁሉ እንዲህ ያለ ስምስ አይገባም ስምህ ተክለ ማርያም ይባል እንጂ አንተ ሕፃን ነህና አሉት፡፡ በዚህም የተነሣ ባለ ሁለት ስም ሆነ፡፡ ቅኔንና የጥበብ መጻሕፍት፣ተግሳጽንም ጾምና ጸሎትን ሥዕል መሳልን መጽሐፍ መጻፍን ሁሉ ተማረ፣ በመንፈሳዊ ሥራ ሁሉ ፍጹም ሆነ፡፡

ጻድቁ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከተጋደሉት ብዙ ትሩፋት እና ከተሰጣቸው ቃልኪዳን ባሻገር በሠዓሊነታቸው በስም ከሚታወቁ እና በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ቤተመንግሥት ቅዱሳት ሥዕላትን ከሚሥሉ ኢትዮጵያውን ሠዓሊያን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእርሳቸው ዘመንም ሌላ በስም የሚታወቀው ፍሬ ጽዮን የተባለ መነኩሴ ሠዓሊ ነው።

  • ጻድቁ አቡነ መብዓ ጸዮን  የሥነ ስቅለትን አሣሣል ዘይቤ ወደ ሀገራችን በስፋት እንዲተዋወቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ተብሎ ይገመታል። ምንም እንኳ በእርሳቸው የተሣለ የስነ ስቅለት ባለገኘም ጻድቁ በእጃቸው የሣሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ለማግኘት ችያለሁ፡፡
በአቡነ መብአ ጽዮን የተሣለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል
በአቡነ መብአ ጽዮን የተሣለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል

በአቡነ መብአጽዮን የተሣለው ይህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል የገበታ ሥዕል ሲሆን ከሥዕሉ በላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ጴጥሮስና ጳውሎስ ጋር ይታያል፡፡ በዚህ ሥዕል ላይ አቡነ መብአ ጽዮን ስማቸውን በተማህጽኖ መልክ እንደ ፍሬ ጽዮን ፈርመው እናገኛለን፡፡ ‹‹ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎቱ ኤላሳቤጥንና እኔ ኃጥኡና ሠዓሊውን ተክለማርምን (አቡነ መብአ ጽዮንን) ይጠብቅ፡፡ ሥዕሉን ያሳለውን ዜና ሐዋርያት አይርሳ፡፡ ሰላም ለጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት፤ የአንተ አማላጅነት ጋሻና ሞገስ ይሁነን፡፡ አሜን፡፡›› 

ጻድቁ ጌታችን በዕለተ ዓርብ መራራ ሐሞት መጠጣቱን አስታውሰው ሁልጊዜ ዐርብ ዐርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር፡፡ መድኃኔዓለምም በየጊዜው በሕፃን አምሳል ይገለጥላቸዋል፡፡ በዕለተ ዓርብም እንደተሰቀለ ሆኖ ይገለጥላቸው ነበር፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ለአቡነ መባዓ ጽዮን በመሠዊያው ላይ በነጭ በግ አምሳል ይገለጥላቸው ነበር፡፡ መከራ ሞቱን እያስታወሱ ሰውነታቸውን ይጎዱ እንደነበር በቅዱስ ገድላቸው ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡-

‹‹በተቀደሰች በዓርባ ጾምም የመድኃኔዓለምን ግርፋት እያሰበ ሰውነቱን በእጅጉ ገረፈ፡፡ ደሙ ከመሬት እስኪወርድ ድረስ ልቡንም አጥቶ ከምድር ላይ ወደቀ፡፡ የመድኃኔዓለምን መከራውን አስቦ እንደሞተም ሆነ፡፡ መድኃኔዓለምም ወደ እርሱ መጣና ‹ተነሥ እኔ ቁስልህን እፈውስሃለሁ› ብሎ የጀርባውን ቁስል ዳሰሰው፡፡ ምንም ሕማም እንዳላገኘውም ሆነ፡፡ መድኃኔዓለምም አባታችንን ‹በአንተው እጅ ትገደልን? እኔ እንኳ የተገደልኩት በአመፀኞች በአይሁድ እጅ ነው› አለው፡፡ በዚያችም ሰዓት ጌታ የመባዓ ጽዮንን ከንፈሮቹን ይዞ ሦስት ጊዜ እፍ አለበትና ‹የከበረ ትንፋሼም ከትንፋስህ ጋራ ይጨመር፣ ሥጋህም ከነፍስህ ጋራ የከበረ ይሁን› አለው፡፡ ‹አንተ በላዩ እፍ ያልህበትም የተቀደሰና የከበረ ይሁን› አለው፡፡››

አቡነ መብዓ ጽዮን በበትራቸው ነፍሳትን ከሲኦል ሲያወጡ
አቡነ መብዓ ጽዮን በወርቅ በትራቸው ነፍሳትን ከሲኦል ሲያወጡ

ጌታችን ለአቡነ መብዓ ጽዮን የወርቅ በትር ሰጥቷቸው በእርሷ ነፍሳትን ከሲኦል ያወጡባት ነበር፡፡ መቋሚያዋም እሳቸው ካረፉ በኋላ የሚሞተውን ሰው እየለየች ትናገር ነበር፡፡ አባታችን እንደ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በመልአክ ተጥቀው ተወስደው የሥላሴን መንበር ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር አጥነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱሱን የሚወክለው ሥዕል ላይ ነፍሳትን በዚህች በትር ሲያወጡ ይሣላል፡፡

አቡነ መብዓ ጽዮን ለልጆቻቸው እንዲህ ብለውም መከረዋል

‹‹ክርስቲያኖች ሁሉ የፈጣሪያችንን የመድኃኔዓለም ክርስቶስን የመታሰቢያ በዓሉን እናድርግ፡፡ የአባቶቻችን የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት መታሰቢያቸው ባረፉበት በተሾሙበት ቀን ይከበራል፡፡ እነርሱን የፈጠራቸው እርሱ መድኃኔዓለም ነው፣ ያከበራቸው፣ ከፍ ከፍ ያደረጋቸው፣ ስማቸውን ለጠራ መታሰቢያቸውን ያደረገ እንደሚድን ቃልኪዳን የሰጣቸው እርሱ ነው፡፡ የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ ያደረገ ግን የተኮነኑ ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣ በሞቱም ጊዜ ሥቃይን አያያትም፡፡›› 

የአቡነ መብዓ ጽዮን በዓለ ዕረፍታቸውም እጅግ አብዝተው በሚዘክሩበትና ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ታስቦ በሚውለው በመድኃኔዓለም ቀን ጥቅምት ሃያ ሰባት ነው፡፡ በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን፡፡

የመድኃኔዓለም ቸርነት የእመቤታችን አማለጅነት እና የጻድቁ ረድኤት ከሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ጋር ለዘላለሙ ጸንቶ ይኑር አሜን፡፡

Photograph copyright © 2005 Michael Gervers, Ewa Balicka-Witakowska, et al.

© በኃይለማርያም ሽመልስ ጥቅምት 27፡ 2008 ዓ.ም. ተጻፈ፡፡

ምንጮች

ድርሣነ መድኃኔዓለም ወገድለ አቡነ መብዓ ጽዮን። ምዕራፍ 2፡ ቁጥር 16። 136።

Marilyn E. Heldmann. African Zion the sacred art of Ethiopia.143.

‹‹ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት ሥዕላት››፡፡ ኃይለማርያም ሽመልስ፡፡ ገጽ 50፡፡

Frē Seyon: Marilyn E. Heldman. A Fifteenth-Century Ethiopian Painter. African Arts, Vol. 31, No. 4, Special Issue: Authorship in African Art, Part 1(Autumn, 1998), pp. 50-51.

ከገድላት አንደበት-ke gedilat andebet 

†††የመድኃኔዓለም ወዳጅ አባታችን መባዓ ጽዮን (ተክለ ማርያም)††† : ሕሊና በለጠ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s