ሥዕልና መጽሐፍ ቅዱስ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ውድ የዚህ መንፈሳዊ ድረ ገጽ ተከታታዮች በቅርቡ በማኅበራዊ ደረ ገጽ (የፌስቡክ ገጽ) ላይ ከአድማስ ሞላ የተባለ ወንድም ‹‹ስእልና ቅዱሳን ስእላት ልዩነታቸው ምንድን ነው ?›› በማለት ጥያቄ አንስቶ ነበር ሲሆን ለጥያቄው መልስ እንዲሆን፤ በተጨማሪም ይህ ጥያቄ ለሚነሳባቸው ምእመናን መልስ እንዲሆን ይህ ጽሑፍ ለንባብ ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡ click for pdf.

ትርጉም

‹‹ሥዕል›› በቁም መልክ፣ የመልክ ጥላ፣ ንድፍ፣ አምሳል፣ ንድፍ በውኃ፣ በመጽሔት፣ በጥልፍ፣ በስፌት ወይም በቀለም በወረቀት ገዝፎ ተጽፎ ከደብር፣ ከእብን፣ ከእጽ፣ ከማዕድን ታንጦ፣ ተቀርጦ፣ ተሸልሞ፣ አጊጦ የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ነው፡፡›› አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ መዝገበ ቃላት ሐዲስ በማለት ተርጉመውታል፡፡[1]

ዮሐንስ ዘደማስቆ የተባለ ሊቅ ደግሞ ‹‹ሥዕል ውክልና ሲሆን በውስጡ የተመሰለውን (የተወከለውን) ባለቤት የያዘ: ነገር ግን ከተወከለው ከባለቤቱ ጋር ግን የተወሰነ ልዩነት አለው፡፡›› በማለት ያብራራዋል፡፡[2]

ሥዕል ነጠላ ሲሆን ሥዕላት ደግሞ ብዛት ያመለክታል፡፡

በአጠቃላይ ሥዕል እና የሥዕሉ ባለቤት ማለትም በሥዕሉ የተወከለው ባለቤት ተመሳሳይነትና ልዩነት አላቸው፡፡ ተመሳሳይነታቸው ከላይ እንደተገለጸው ሥዕል የአንድ ነገር መልክ፣ የመልክ ጥላ፣ ምሳሌ (አምሳል) ወይም ውክልና ቢሆንም በውስጡ ግን የተመሰለውን (የተወከለውን) ባለቤት የያዘ በመያዙ ነው፡፡

ይህ ሲባል ግን ከተወከለው ከባለቤቱ ጋር ግን የተወሰነ ልዩነት ያለው መሆኑን በመረዳት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የተሣለው ሥዕል ባለቤቱን ቢመስለውም ውክልና እንጂ ባለቤቱ አይደለም ማለት ነው፡፡[3]

ለምሳሌ አንድ ሰው ፎቶግራፍ ቢነሣ ሰውየው የተነሣው ፎቶ (ሥዕል) አለ ራሱም ፎቶው የተነሣው ሰው (ባለቤት) አለ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ይህን አግኝቶ “ይህ ፎቶ ላይ ያለው ማን ነው?” ብሎ ቢጠይቅ መልሱ ‹‹እገሌ/ሊት›› ይሆናል፡፡ መልሱ “እገሌ/ሊት” የሆነው ፎቶው (ሥዕሉ) እና ባለቤቱ አንድ ስለሆኑ አይደለም ነገር ግን ፎቶው ሰውየውን ስለሚወክለው እንጂ፡፡ ምክንያቱም ፎቶው በራሱ ሕይወት የሌለው ወረቀት ስለሆነ ሕይወት ካለው ሰው (ባለቤቱ) ጋር አንድ ሊሆን አይችልም፡፡[4]

በመጽሐፍ ቅዱስ ሦስት ዓይነት ሥዕላት ሲኖሩ እነዚህም ቅዱሳት ሥዕላትርኩሳን ሥዕላት እና ዓለማውያን ሥዕላት ናቸው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ስለቅዱሳት ርኩሳን እና ዓለማውያን ሥዕላት ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና በዘመናችን ከሚገኙ ሁኔታዎች አንጻር ምንነታቸው፣ ዓይነታቸውን እና ልዩነታቸውን በምሳሌ እናያለን፡፡

ቅዱሳት ሥዕላት

ቅዱሳት የሚለው ቃል ደግሞ «ቀደሰ» ከሚለው የግዕዝ ግሥ ሲሆን ትርጉሙም ለየ፣ አከበረ፣ መረጠ ማለት ነው።[5] ከዚህም በመነሳት ቅዱሳት ሥዕላት ለእግዚአብሔር የተለዩ፣ የተቀደሱ ፣ልዩ ፣ ምርጥ፣ ንጹሕ እና ጽሩይ የሆኑ የቤተመቅደሱ መገልገያ ንዋያተ ቅድሳት በመሆናቸው «ቅዱሳት» ተብለው ይጠራሉ።

ዳግመኛም የቅዱሳንን ታሪክ እና ማንነት በጊዜው ላልነበርን በመንፈስ ዓይን እንድናይ ስለሚያደርጉን፤ አንድም ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ ዓለማውያን ሥዕላት ፈጽመው የተለዩ በመሆናቸው፤ አንድም የቅዱሳን ቅድስና ሥዕላቱን ቅዱስ ስላሰኛቸው፤ አንድም በሥዕላቱ አድሮ እግዚአብሔር ስለሚፈጽመው ገቢረ ተአምራት የተነሣ ሥዕላቱ «ቅዱሳት ሥዕላት» ተብለው ይጠራሉ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት ሥዕላት ተብለው የሚጠሩት ሐዋርያዊ ትውፊትንና ቀኖናን ጠብቀው የሚሣሉ የቅዱስ እግዚአብሔር፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የቅዱሳን መላእክት፣ የቅዱሳን ነቢያት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት እና የሌሎች ቅዱሳን ጻድቃን ማንነት፣ ሕይወትና ታሪክ የሚያሳዩ እና የሚወክሉ ሥዕሎች ናቸው፡፡ ዘጸ25፣18-22፤ 37፣7-9፤ዘጸ 26-31፤36፣8-35፡፡ [6]

የቅዱሳት ሥዕላት ምሳሌዎች

ርኩሳን ሥዕላት (ጣዖታት)

ርኩሳን ሥዕላት በመጽሐፍ ቅዱስ የሚባሉት በተለያዩ መልኮች የሚሣሉ ሆነው የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ የሚቃወሙና በተቃራኒው ደግሞ የሰይጣንን ክፉ ተግባራት የሚያወድሱት በሙሉ ናቸው፡፡ በዚህ ዘመንም የጣዖት አምላኪዎች የሚጠቀሙባቸው ሥዕሎች፣ የአምልኮ ምልክቶች እና ጽሑፎች እና ወዘተ. . . ከዚህ መደብ ይገባሉ፡፡

 በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚገኙ ርኩሳን ሥዕሎች መካከል እስራኤላውያን በጥጃና በተለያዩ እንስሳት ምስል ሰርተው ያመልኳቸው የነበሩት ዘፀ 32፡1-10፣ ናቡከደነጾር በባቢሎን አውራጃ በዱር ሜዳ አቁሞት የነበረው ከወርቅ የተሠራ ምስል ዳን 3፡1፣ እና ከነዓውያን ያመልኳት የነበረችው ‹‹ አስታሮት›› የተባለችው የሴት ምስል ወዘተ. . . የመሳሰሉት ርኩሳን ሥዕላት ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህን ርኩሳን ሥዕላት ተብለው ለመጠራታቸው ዘዳ 7፡25፤ 1ኛ ነገ 12፡28-30፤ ዳን 11፡31፤ 12፡11፤ ማቴ 24፡15-18 መመልከት ይቻላል፡፡[7]

እስራኤላውያን ለበአል ለተባለው ጣዖት መስዋእት እንዳቀረቡ
እስራኤላውያን ለበአል ለተባለው ጣዖት መስዋእት እንዳቀረቡ

ዓለማውያን ሥዕላት

ዓለማውያን ሥዕላት የሚባሉት ደግሞ መንፈሳዊ ይዘት የሌላቸው ማንኛውም ዓይነት ሥዕላት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሥዕላት በሕዝበ እስራኤል ሆነ በጣዖት አምላኪዎች በአረማውያን ዘንድ ለአምልኮ የማይጠቀሙባቸው ሥዕላት ናቸው፡፡

እነዚህ ሥዕላት ለዕለት ከዕለት ኑሯቸው የሚጠቀሙባቸው ሥዕሎችን ያካትታል፡፡ ለምሳሌ በተለያዩ ዘመናት በተነሡ ነገሥታት በተሠሩ ሳንቲሞች ላይ የምንመለከታቸው የነገሥታት ሥዕሎች ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፤ ማቴ 22፣20፡፡

ወዳለንበት ዘመን ስንመልሰው ደግሞ ዓለማውያን ሥዕላት የሚባሉት ማንኛውም ዓይነት የሚታይና ወካይ የሆነ ነገር ግን ለአምለኮ የማይውል ሥዕሎችን በሙሉ ሚያካትት ነው፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ አካላት ፎቶዎችን፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች (ቢንቀሳቀሱም የብዙ ሥዕሎች ውጤት በመሆናቸው)፣ የማንኛውም ቋንቋ ፊደላት (ሆሄያትም ቢሆኑ በእጅ የሚጻፉ ሥዕሎች ናቸው[8])፣ የተለያዩ አካላት አንድን ሀሳብ ለማስተላለፍ የሚጠቀሙባቸው ውክልና ምልክቶች (የትራፊክ ምልክቶች፣ የድርጅቶች ዓርማ፣ ወዘተ. . .)፣ የተለያዩ የመዋብያና ማስጌጫ ጌጣጌጦችን (ንቅሳትን፣ በእቃዎች ላይ የሚታዩ ሐረጋትን ወዘተ. . .) ያጠቃላል፡፡

የቀድሞው የቤተክርስቲያናችን ፓትርያርክ ብፁእ አቡነ ተክለሃይማነኖት ከቤተክርስቲያን ከጳጳሳትና ከሊቃውነት ጋር ሆነው የተነሡት ፎቶ
የቀድሞው የቤተክርስቲያናችን ፓትርያርክ ብፁእ አቡነ ተክለሃይማኖት ከቤተክርስቲያን ከጳጳሳትና ከሊቃውነት ጋር ሆነው የተነሡት ፎቶ
Coin of the Axumite king Gersem
የቁም ምልክት

በመጨረሻም የወንድሜን ጥያቄ ለመመለስ ሥዕል የአንድ ነገር ምስሌ ውክልና ሲሆን ቅዱሳት ሥዕላት ደግሞ ከሥዕል አንዱ ወገን ናቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን ሁሉም ሥዕል ቅዱሳት ናቸው፣ አሊያም ዓለማውያን ሲቀጥልም ርኩሳን ናቸው ማለት አይደልም፡፡ ነገር ግን የሚወክሉት አካልና የሚውሉበት ዓለማ የሥዕሉን ወገን ይገልጻል እንጂ፡፡

በዚህ ጽሑፍ የሥዕል ዓይነቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር የተመለከትን ሲሆን በሚቀጥለው ጽሑፍ የቅዱሳት ሥዕላት ዓይነቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ዮሐንስ ዘደማስቆ ካስተማረው በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡ የከርሞ ሰው ይበለን፡፡

© ከኃይለማርያም ሽመልስ ሰኔ 2007 ዓ.ም.


ዋቢ መረጃዎች

[1] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት።673፡፡

[2] Mary H. Allies. Jhon Damascene on holy Images, Apologia of St. John Damascene Against Those Who Decry Holy Images Part three. 92.

[3] ኃይለማርያም ሽመልስ፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት ሥዕላት፡  ታሪክ፣ መንፈሳዊ ትርጉም፣ የሊቃውንት አስተምህሮ እና ሌሎችም. . .፡፡ 120፡፡

[4] ኃይለማርያም ሽመልስ፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት ሥዕላት፡  ታሪክ፣ መንፈሳዊ ትርጉም፣ የሊቃውንት አስተምህሮ እና ሌሎችም. . .፡፡ 120፡፡

[5] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት።784፡፡

[6] መ/ር ኃይለማርያም ላቀው፡፡ ሐውልተ ሰምዕ፡፡ 144፡፡

[7] አበበ ጋሻዬ፡፡ ትምህርተ ተዋሕዶ፡፡ 64፡፡

[8] በዚህ ርእስ ሰፋ ያለ ትንታኔ በሚቀጥሉት ጽሑፎች ይቀርባል፡፡

One thought on “ሥዕልና መጽሐፍ ቅዱስ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s